ለ45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የልዑካን ቡድን የማበረታቻና የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

መጋቢት 24/2016 ዓ.ም

ማርች 30/2024 በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው 45ኛ የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካፍሎ በሁለት ወርቅ ፣ በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከዓለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ በድል ለተመለሰው የልዑካን ቡድን ዛሬ መጋቢት 24/2016 ዓ.ም በቤልቪው ሆቴል የእውቅናና የማበረታቻ መርሃ ግብር ተከናወነ፡፡

በመርሀግብሩ መጀመሪያ አትሌቶችን በመወከል አትሌት ማርታ አለማየሁ እና አትሌት በሪሁ አረጋዊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በውድድሩ የገጠማቸውን ዝርዝር አብራርተው ፤ የተመዘገበው ድል የተሻለ መሆኑን እና ቀጣይ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የቡድኑ መሪና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ተስፋዬ አስግዶም እና የቡድኑ ቴክኒክ መሪና የኢ.አ.ፌ የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተሩ አቶ አስፋው ዳኜ በየተራ ስለነበራቸው የውድድር ቆይታ ያብራሩ ሲሆን ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ላደረጉት ሁለተናው ድጋፍ በልዑካኑ ስም ምስጋና ተችሮታል፡፡

አሰልጣኞችን በመወከል ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ በአዋቂዎች ምድብ ባይሳካላንም በታዳጊዎች ወጣት ሴቶች ተከታትለው በመግባት ኢትዮጵያ ተተኪ እንዳላት ያሳዩ ሲሆን ካለፈው ተምረን ነገ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ አመላካች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን አትሌቶች የተቻላቸውን ሰርተዋል በዚህ ውድድር የምንማርበት እና እራሳችንን ለኦሎምፒክ የምንፈትሽበት ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ም/ፀሃፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ስለመጣው ውጤት ምስጋናቸውን በማቅረብ ለቀጣይ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም በቅርቡ አትሌቶች እና ባለሞያች ወደ ሆቴል የማስገባት ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማገባደጃ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን በመግለፅ ለቀጣይ ውድድሮች ላይ ትኩረት ተደረጎ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል አክለውም በተለይ አገራችን በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከአሁኑ በቂ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት በመግለፅ ለዚህ ውድድር መሳካት ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ ለሰሩ ባለድርሻ አካላትን በቡድኑና ስም ምስጋና አቅርበዋል ፡፡

በመጨረሻም የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዘዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን አትሌቶችን በማበረታታት ከፌዴሬሽኑ ጋር አብረን በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል

👉ፌዴሬስኑ ለልዑካን ቡድኑ በመመሪያው እና በአሰራሩ መሰረት የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አበርክቶላቿል፡፡